← Back to Press Center
OTHERSACTIVE2026-10-16

እረኝነት፣ ስብከተ ወንጌልና ድኅነተ ነፍሳት

እረኝነት፣ ስብከተ ወንጌልና ድኅነተ ነፍሳት


(ቅ.ሥ.ዩ ጥቅምት 6 ቀን 2019 ዓ.ም)


የቤተ ክርስቲያን እውነተኛ ሀብት በገንዘብና በቁሳዊ ንብረት ብቻ ሳይሆን፣ በወንጌል ወደ ክርስትና በሚመለሱና በእምነታቸው በሚጸኑ ሕዝበ ክርስቲያኖች ሕይወት ይገለጣል። የአንድ ሊቀ ጳጳስ የእረኝነትና ስብከተ ወንጌል ኃላፊነትም በተመደበበት ሀገረ ስብከት (ሕዝበ ክርስቲያን) በመንፈሳዊ እንክብካቤ፣ በማስተማር፣ በመምራትና የወንጌልን ብርሃን ወዳልደረሰባቸው አካባቢዎች ማድረስ መሆኑ ይታወቃል።


በ45ኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ስብሰባ ላይ የቀረበው ሪፖርት በደቡብ ኦሞና አሪ ዞኖች ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት በተከናወነው “ዘመቻ ፊልጶስ” የተመዘገበውን ውጤት፤ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ (ዶ/ር) ለሚመሩት ሕዝብ ያላቸውን የእረኝነት ኃላፊነት የሚያሳይ ነው።


የእረኝነት ስኬት የሚለካው በስብከተ ወንጌል በሚመለሱ ነፍሳት ብዛትና በሚጸኑበት የእምነት ሕይወት ዋነኛው መሆኑን የሚያሳየን በደቡብ ኦሞና አሪ ዞኖች ሀገረ ስብከት

በ180 የስብከተ ወንጌል ጉባኤያት 23,199 አላማኝ ሕዝብ ወደ ቅድስት ቤተክርስቲያን መመለሳቸው አይነተኛ ምስክራችን ነው።

------------


“ዘመቻ ፊልጶስ” በሚል ስያሜ በደቡብ ኦሞና አሪ ዞኖች ሀገረ ስብከት በተካሄዱ 180 የወንጌል ጉባኤያት 23,199 አሕዛብ ወደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት መመለሳቸው ተገለጸ።


ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ (ዶ/ር)፣ የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትና የደቡብ ኦሞና አሪ ዞኖች ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ወንጌል በአካባቢው እንዲስፋፋና ለሕዝቡ የበለጠ ተደራሽ እንዲሆን ባላቸው ፍላጎት መሠረት፣ “ዘመቻ ፊልጶስ” በሚል ርዕስ ስብከተ ወንጌልን ለማጠናከር የተቀናጁ ሐዋርያዊ እንቅስቃሴዎች ተከናውነዋል።


በዚህ ሐዋርያዊ እንቅስቃሴ በተለይም ዓቢይ ጾምን ምክንያት በማድረግ፣ የሀገረ ስብከቱ ሠራተኞች፣ የአብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎች: ሰባክያን ወንጌል: መንፈሳዊያን ማኅበራትና ሰ/ትምህርት ቤቶች በቅንጅት በመሥራት በተለያዩ አካባቢዎች 180 የስብከተ ወንጌል ጉባኤያትን አካሂደዋል። በእነዚህ ጉባኤያት በተደረገው የሰብከተ ወንጌል አገልግሎት፣ ከተለያየ የእምነት ሕይወት 23,199 ወደ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መመለሳቸው ተገልጿል።


የዘመቻው አንዱ ዋና መለያ በሁለት ጽዋዎች (ዋንጫዎች) አማካይነት ስብከተ ወንጌልን ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ማድረስ ነበር። የመጀመሪያውን ጽዋ (ዋንጫ) በጂንካ ከተማ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት በማዘዋወር ልዩ ሐዋርያዊ አገልግሎት ተከናውኖበታል። ሁለተኛው ጽዋ (ዋንጫ) ደግሞ በወረዳዎችና የወንጌል ጉባኤ አይተው የማያውቁ የገጠር ከተሞች ድረስ በመድረስ ሰፊ የስብከተ ወንጌል ንቅናቄ እንዲፈጠር አስችሏል።


ይህ ውጤት የስብከተ ወንጌልን አገልግሎት በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ ለማካሄድ የተደረገውን ጥረት የሚያሳይ ሲሆን፣ በተለይም ወንጌል በብዛት ወዳልደረሰባቸው አካባቢዎች ሐዋርያዊ አገልግሎት መድረሱን ያመለክታል። የሀገረ ስብከቱ አገልጋዮች በጋራ ያከናወኑት ይህ ተግባር የወንጌልን መልእክት ለማስፋፋትና በአካባቢው የመንፈሳዊ ሕይወት እድገትን ለማጠናከር ያለውን ትልቅ ትርጉም ያሳያል።


የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ መላው ማኅበረ ሰብም በዩኒቨርሲቲያችን ፕሬዚደንትና የደቡብ ኦሞና አሪ ዞኖች ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ (ዶ/ር) በሀገረ ስብከታቸው ባስመዘገቡት ሐዋርያዊ ተልዕኮ ውጤት የተሰማውን ደስታ ይገልጻል።

More Stories

Our Latest Publishings

Holy Trinity University

Holy Trinity
University

The Orthodox Theology is the experience of the communion opened by Jesus Christ, affirming the truth of teaching about the mystical communion, fundamental to knowing God.

Legal

Contact

Addis Ababa, Ethiopia
+251 111 233 528+251 111 233 528
president-office@htu.edu.et

Newsletter

Stay updated with our latest news, events, and academic publications.

Š 2026 Holy Trinity University. All rights reserved.

A ministry of the Ethiopian Orthodox Tewahido Church