← Back to Press Center
OTHERSACTIVE2026-10-21

የሩሲያ እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት የጋራ ኮሚሽን 4ኛ ጉባኤውን በሞስኮ አካሄደ::

የሩሲያ እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት የጋራ ኮሚሽን 4ኛ ጉባኤውን በሞስኮ አካሄደ 


(ቅ.ሥ.ዩ. ጥቅምት 9፣ 2019 ዓ.ም) 


በሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መካከል ያለው የጋራ ኮሚሽን 4ኛ መደበኛ ጉባኤውን በሩሲያ መዲና ሞስኮ አካሂዷል። ይህ ከፍተኛ የሁለትዮሽ የምክክር ጉባኤ የተካሄደው የሞስኮ እና የመላው ሩሲያ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ኪሪል እንዲሁም የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በሰጡት አባታዊ ቡራኬ እና መመሪያ መሆኑ ተገልጿል። በአብያተ ክርስቲያናት ቅዱሳን አባቶች ቡራኬ የተወከሉት የሁለቱም ወገን ልዑካን በወንድማማችነት እና በጋራ የትብብር መንፈስ የሁለትዮሽ ውይይቱን በስኬት አከናውነዋል።


በጉባኤው ላይ የሞስኮ ፓትርያርክን በመወከል የሴርጊየቭ ፖሳድ እና ዲሚትሮቭ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኪሪል የሁለትዮሽ ጉባኤውን በጥምር ሰብሳቢነት የመሩት ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በመወከል ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ (ዶ/ር፣ ተ/ፕ/ር) የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት፣ የደቡብ ኦሞና አሪ ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሰብሳቢነት ልኡካኑን መርተዋል። በሩሲያ ቤተ ክርስቲያን በኩል የክርስቲያኖች አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ግንኙነት ጸሓፊ የሆኑት አባ እስጢፋኖስ፣ የማርታ እና ማርያም ገዳም እመ ምኔት እማሆይ ኤልሳቤጥ (ፖዝድንያኮቫ)፣ የአብያተ ክርስቲያናት እና ሚዲያ ግንኙነት መምሪያ ምክትል ኃላፊ ቫክታንግ ኪፕሺዜ እና ሰርጌይ አልፌሮቭ የተሳተፉ ሲሆን፤ የሞስኮ ፓትርያርክ ምክትል ቻንስለር ብፁዕ አቡነ ሲልዋን በእንግድነት ተገኝተዋል። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በኩል ደግሞ የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ምክትል ፕሬዝደንት ፕሮፌሰር አባ ኃይለ ገብርኤል ግርማ እንዲኹም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በመንበረ ፓትርያርክ የቅዱስ ሲኖዶስ ኮሙኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ ቀሲስ ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል በጉባኤው ላይ ተሳትፈዋል።


ተሳታፊዎቹ በ3ኛው ጉባኤ ወቅት የተያዙ ዕቅዶችን አፈጻጸም የገመገሙ ሲሆን በጉባኤው ማጠቃለያ ላይም የሁለቱን አብያተ ክርስቲያናት ታሪካዊና ዘላቂ ግንኙነት የሚያጸና የጋራ መግለጫ አውጥተዋል። በውይይቱም ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ በክርስቲያኖች ላይ የሚደርሱ ጫናዎችን የመከላከል ጉዳይ ዋና ትኲረት ተሰጥቶታል፡፡ በጉባኤው ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዩክሬን እና በምሥራቅ አውሮፓ በሚገኙ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ካህናት እና ምዕመናን ላይ የሚደረገውን ስደት የምትቃወም መሆኗን ገልጻለች። በተመሳሳይ መልኩ የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎች ጥቃት ለሚደርስባቸው የተዋሕዶ ምዕመናን ያላትን ጥብቅ ድጋፍ ያረጋገጠች ሲሆን ሁለቱም አብያተ ክርስቲያናት ሃይማኖት ለፖለቲካ ጥቅም መዋሉን አጥብቀው ኮንነዋል።


በሌላ በኩል ሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት በትምህርት፣ በሚዲያ፣ በቤተ ክርስቲያን ሥነ ጥበባት እና በሰብኣዊ አገልግሎት ዘርፎች ያላቸውን ትብብር ለማስፋፋት ተስማምተዋል። በዚህም መሠረት የሞስኮ ነገረ መለኮት ትምህርት ቤት የኢትዮጵያ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዝግጁነቱን ያረጋገጠ ሲሆን በሦስተኛ (በዶክትሬት) ዲግሪ መርሐ ግብራት፣ በትምህርት ጽሑፍ ህትመቶች እና በኢትዮጵያ ጥናቶች ዙሪያ ከሩሲያ ሳይንስ አካዳሚ ጋር በጋራ ለመሥራት ከስምምነት ተደርሷል። ከዚህ በተጨማሪ በሞስኮ በሚገኘው የቅዱስ አሌክሲስ ማዕከላዊ ሆስፒታል፣ በአዲስ አበባ በሚገኘው ምግባረ ሠናይ ሆስፒታል እና በደጃዝማች ባልቻ የሩሲያ ቀይ መስቀል ሆስፒታል መካከል የማኅበራዊ እና የሕክምና አገልግሎት ትብብር የሚያደረግ ሲሆን በሁለቱ ሀገራት የሚገኙ ቅዱሳት መካናትን የሚያስተሳስሩ መንፈሳዊ ጉዞዎችን እንደገና ለማስጀመር እና በገዳማውያን መካከልም የጋራ የልምድ ልውውጥ ለማድረግ መወሰኑ ተገልጿል።


የዚህ የ4ኛው ጉባኤ ውሳኔዎች እና የመጨረሻ ስምምነቶች ለሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት ቅውዱሳን ፓትርያርኮች እና ቅዱሳን ሲኖዶሶች ለምክክርና ለውሳኔ የሚቀርቡ ሲሆን፤ ኮሚሽኑ 5ኛ መደበኛ ጉባኤውን በ2028 (እ.አ.አ.) በኢትዮጵያ ለማካሄድ ወስኖ ስብሰባውን አጠናቅቋል።


የዜናው ምንጭ፡- https://mospat.ru/en/news/94560/

More Stories

Our Latest Publishings

Holy Trinity University

Holy Trinity
University

The Orthodox Theology is the experience of the communion opened by Jesus Christ, affirming the truth of teaching about the mystical communion, fundamental to knowing God.

Legal

Contact

Addis Ababa, Ethiopia
+251 111 233 528+251 111 233 528
president-office@htu.edu.et

Newsletter

Stay updated with our latest news, events, and academic publications.

Š 2026 Holy Trinity University. All rights reserved.

A ministry of the Ethiopian Orthodox Tewahido Church